ምሳሌ 13:7-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ምንም ሳይኖረው ባለጠጋ መስሎ የሚታይ ሰው አለ፤ሌላው ድኻ መስሎ ይታያል፤ ግን ብዙ ሀብት አለው።

8. የሰው ሀብቱ ለሕይወቱ ቤዛ ሊሆነው ይችላል፤ድኻው ግን ሥጋት የለበትም።

9. የጻድቃን ብርሃን ደምቆ ይበራል፤የክፉዎች መብራት ግን ይጠፋል።

10. ትዕቢት ጠብን ብቻ ያስፋፋል፤ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ትገኛለች።

11. ያላግባብ የተገኘ ገንዘብ እየተመናመነ ያልቃል፤ገንዘቡን ጥቂት በጥቂት የሚያከማች ግን ይጠራቀምለታል።

12. ለነገ የሚባል ተስፋ ልብን ያሳምማል፤የተሳካ ምኞት ግን የሕይወት ዛፍ ነው።

13. ምክርን የሚያቃልል በራሱ ላይ ጥፋት ያመጣል፤ትእዛዝን የሚያከብር ግን ወሮታን ይቀበላል።

14. የጠቢብ ትምህርት የሕይወት ምንጭ ናት፤ሰውን በሞት ወጥመድ እንዳይያዝ ታደርገዋለች።

15. መልካም ማስተዋል ሞገስን ታስገኛለች፤የከዳተኞች መንገድ ግን አስቸጋሪ ነው።

16. አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል፤ተላላ ግን ሞኝነቱን ይገልጣል።

17. ክፉ መልእክተኛ መከራ ውስጥ ይገባል፤ታማኝ መልእክተኛ ግን ፈውስን ያመጣል።

ምሳሌ 13