ምሳሌ 12:4-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት፤አሳፋሪ ሚስት ግን ዐጥንቱ ውስጥ እንዳለ ንቅዘት ናት።

5. የጻድቃን ሐሳብ ቀና ነው፤የክፉዎች ምክር ግን ሸር አለበት።

6. የክፉዎች ቃል ደም ለማፍሰስ ታደባለች፤የቅኖች ንግግር ግን ይታደጋቸዋል።

7. ክፉ ሰዎች ይገለበጣሉ፤ ድራሻቸውም ይጠፋል፤የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።

8. ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፤ጠማማ ልብ ያላቸው ግን የተናቁ ናቸው።

9. የሚበላው ሳይኖረው ከሚኵራራ ይልቅ፣ራሱን ዝቅ አድርጎ ሠራተኛ የሚያሳድር ይሻላል።

10. ጻድቅ ሰው ለእንስሳቱ ይራራል፤ክፉዎች ራሩ ቢባል እንኳ ዞሮ ዞሮ ሥራቸው ጭካኔ ነው።

11. መሬቱን የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤ከንቱ ተስፋን የሚያሳድድ ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል።

12. ኀጥኣን የክፉዎችን ምርኮ ይመኛሉ፤የጻድቅ ሥር ግን ይንሰራፋል።

13. ክፉ ሰው በእኩይ ንግግሩ ይጠመዳል፤ጻድቅ ሰው ግን ከመከራ ያመልጣል።

14. ሰው ከከንፈሩ ፍሬ የተነሣ በበጎ ነገር ይሞላል፤እንደ እጁ ሥራም ተገቢውን ዋጋ ያገኛል።

15. ተላላ ሰው መንገዱ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤ጠቢብ ሰው ግን ምክር ይሰማል።

16. ተላላ ሰው ቊጣው ወዲያውኑ ይታወቅበታል፤አስተዋይ ሰው ግን ስድብን ንቆ ይተዋል።

17. ሐቀኛ ምስክር በእውነት ይመሰክራል፤ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸት ይናገራል።

18. ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል።

19. እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤ሐሰተኛ አንደበት ግን ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው።

20. ክፋትን በሚያውጠነጥኑ ሰዎች ልብ አታላይነት አለ፤ሰላምን የሚያራምዱ ግን ደስታ አላቸው።

ምሳሌ 12