ምሳሌ 12:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ተግሣጽን የሚወድ ዕውቀትን ይወዳል፤መታረምን የሚጠላ ግን ደነዝ ነው።

2. መልካም ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ያገኛል፤ተንኰለኛውን ግን እግዚአብሔር ይፈርድበታል።

3. ሰው በክፋት ላይ ተመሥርቶ ሊጸና አይችልም፤ጻድቃን ግን ከቦታቸው አይነቃነቁም።

4. መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት፤አሳፋሪ ሚስት ግን ዐጥንቱ ውስጥ እንዳለ ንቅዘት ናት።

5. የጻድቃን ሐሳብ ቀና ነው፤የክፉዎች ምክር ግን ሸር አለበት።

6. የክፉዎች ቃል ደም ለማፍሰስ ታደባለች፤የቅኖች ንግግር ግን ይታደጋቸዋል።

7. ክፉ ሰዎች ይገለበጣሉ፤ ድራሻቸውም ይጠፋል፤የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።

8. ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፤ጠማማ ልብ ያላቸው ግን የተናቁ ናቸው።

9. የሚበላው ሳይኖረው ከሚኵራራ ይልቅ፣ራሱን ዝቅ አድርጎ ሠራተኛ የሚያሳድር ይሻላል።

10. ጻድቅ ሰው ለእንስሳቱ ይራራል፤ክፉዎች ራሩ ቢባል እንኳ ዞሮ ዞሮ ሥራቸው ጭካኔ ነው።

11. መሬቱን የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤ከንቱ ተስፋን የሚያሳድድ ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል።

12. ኀጥኣን የክፉዎችን ምርኮ ይመኛሉ፤የጻድቅ ሥር ግን ይንሰራፋል።

13. ክፉ ሰው በእኩይ ንግግሩ ይጠመዳል፤ጻድቅ ሰው ግን ከመከራ ያመልጣል።

ምሳሌ 12