12. ጥላቻ ጠብን ያነሣሣል፤ፍቅር ግን ስሕተትን ሁሉ ይሸፍናል።
13. ጥበብ በአስተዋይ ሰው ከንፈር ትገኛለች፤በትር ግን ማመዛዘን ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው።
14. ጠቢባን ዕውቀት ያከማቻሉ፤የተላላ አንደበት ግን ጥፋትን ይጋብዛል።
15. የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤ድኽነት ግን የድኾች መጥፊያ ናት።
16. የጻድቃን ደመወዝ ሕይወት ታስገኝላቸዋለች፤የክፉዎች ትርፍ ግን ቅጣትን ታመጣባቸዋለች።
17. ተግሣጽን ነቅቶ የሚጠብቅ የሕይወትን መንገድ ያሳያል፤ዕርምትን የማይቀበል ግን ሌሎችን ወደ ስሕተት ይመራል።
18. ጥላቻውን የሚሸሽግ ሐሰተኛ አንደበት ያለው ነው፤ሐሜትን የሚዘራ ሁሉ ተላላ ነው።
19. ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው።
20. የጻድቅ አንደበት የነጠረ ብር ነው፤የክፉ ሰው ልብ ግን ርባና የለውም።
21. የጻድቃን ከንፈሮች ብዙዎችን ያንጻሉ፤ተላሎች ግን ከማመዛዘን ጒድለት ይሞታሉ።