6. ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው’ ብሎ፣ ሽባውን፣ ‘ተነሣ! ቃሬዛህን ይዘህ ወደ ቤትህ ሂድ’ ” አለው።
7. ሽባውም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ሄደ።
8. ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተደነቁ፣ በፍርሃት ተሞልተው፣ እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
9. ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው በቀረጥ ማስከፈያ ኬላ ተቀምጦ አየ፤ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።
10. ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ላይ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ሊበሉ ተቀመጡ።
11. ፈሪሳውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋር እንዴት አብሮ ይበላል?” ብለው ጠየቋቸው።