ማቴዎስ 7:14-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን፣ በሩም ጠባብ ነው፤ የሚገቡበትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው።

15. “በውስጣቸው ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው መካከላችሁ በመግባት ከሚያሸምቁ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።

16. ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ ቍጥቋጦ ወይን፣ ከኵርንችትስ በለስ ይለቀማልን?

17. እንዲሁም ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ፣ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል።

18. ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ፣ መጥፎም ዛፍ ጥሩ ፍሬ ማፍራት አይችልም።

19. ጥሩ ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል።

20. ስለዚህ በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ።

21. “በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም።

22. በዚያ ቀን ብዙዎች፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል።

23. በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ።

24. “እንግዲህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል፣ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራን ብልኅ ሰው ይመስላል።

25. ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንን ቤት መታው፤ በዐለት መሠረትም ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።

26. ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውለው ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል።

27. ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንን ቤት መታው፤ ቤቱም ወደቀ፤ አወዳደቁም የከፋ ነበር።”

28. ኢየሱስ ማስተማሩን በፈጸመ ጊዜ፣ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ።

29. ምክንያቱም እንደ አይሁድ ሃይማኖት መምህራናቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን አስተምሮአቸው ስለ ነበር ነው።

ማቴዎስ 7