22. እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቈጣ ይፈረድበታል፤ ማንም ወንድሙን ‘ጅል’ የሚል በሸንጎ ፊት ይጠየቅበታል፤ ‘ደደብ’ የሚለው ደግሞ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይጠብቀዋል።
23. “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣
24. መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ።
25. “የከሰሰህ ባላጋራህ እንዳያስፈርድብህ፣ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ እንዳይሰጥህ፣ በወህኒም እንዳትጣል፣ በመንገድ ላይ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ።
26. እውነት እልሃለሁ፤ ካስፈረደብህ ግን የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።
27. “ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
28. እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል።
29. ቀኝ ዓይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።
30. ቀኝ እጅህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።
31. “ ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ ወረቀት መስጠት አለበት’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
32. እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በላዩ ላይ ስታመነዝር ካላገኛት በስተቀር፣ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ በዚህ ሁኔታ የተፈታችውን ሴት ያገባም እንዳመነዘረ ይቈጠራል።
33. “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘በሐሰት አትማል፤ በእግዚአብሔር ፊት የማልኸውንም ጠብቅ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
34. እኔ ግን ፈጽሞ አትማሉ እላችኋለሁ፤ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤
35. በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና
36. በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከጠጕራችሁ መካከል አንዲቷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቍር ማድረግ አትችሉምና።
37. ስለዚህ ስትነጋገሩ ቃላችሁ፣ ‘አዎን’ ከሆነ፣ ‘አዎን’፤ አይደለም፣ ከሆነ ‘አይደለም’ ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ከክፉው የሚመጣ ነውና።