ማቴዎስ 27:54-66 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

54. የመቶ አለቃውና አብረውት ኢየሱስን ይጠብቁት የነበሩት የመሬት መናወጡንና የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው፤ ይህስ፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አሉ።

55. ከገሊላ የመጡና ኢየሱስን በሚያስፈልገው ነገር ለማገልገል የተከተሉት ብዙ ሴቶች ሁኔታውን ከርቀት እየተመለከቱ በአካባቢው ነበሩ።

56. ከእነርሱም መካከል ማርያም መግደላዊት፣ ማርያም የያዕቆብና የዮሴፍ እናት እንዲሁም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ።

57. ምሽት ላይ ዮሴፍ የሚባል ሀብታም ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱ ራሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ።

58. ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስን በድን ለመነው፤ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ።

59. ዮሴፍም በድኑን ወስዶ በንጹሕ የበፍታ ጨርቅ ከፈነው፤

60. ለራሱ ከዐለት አስፈልፍሎ ባዘጋጀው መቃብር ውስጥ አኖረው፤ ከዚያም ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ የመቃብሩን በር ዘግቶ ሄደ።

61. በዚህ ጊዜ ማርያም መግደላዊትና ሌላዋ ማርያም ከመቃብሩ ትይዩ ተቀምጠው ነበር።

62. በማግሥቱ፣ ከሰንበት ዝግጅት በኋላ ባለው ቀን፣ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ጲላጦስ ፊት ቀርበው እንዲህ አሉት፤

63. “ክቡር ሆይ፤ ያ አሳች በሕይወት ሳለ፣ ‘ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ’ ያለው ትዝ ብሎናል፤

64. ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ አስከሬኑን ሰርቀው ለሕዝቡ፣ ‘ከሙታን ተነሥቶአል’ ብለው እንዳያስወሩ መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ ትእዛዝ ስጥልን፤ አለዚያ የኋለኛው ስሕተት ከፊተኛው የባሰ ይሆናል!”

65. ጲላጦስም፣ “ጠባቂዎች አሏችሁ፤ ሄዳችሁ በምታውቁት መንገድ አስጠብቁ” አላቸው።

66. እነርሱም ሄደው መቃብሩን በማኅተም አሽገው ጠባቂ አቆሙበት።

ማቴዎስ 27