ማቴዎስ 27:43-55 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

43. በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ይል ስለ ነበር እስቲ ከወደደው አሁን ያድነው!”

44. ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎችም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር።

45. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።

46. በዘጠኝ ሰዓት ገደማ፣ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” እያለ ጮኸ፤ ትርጕሙም “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው።

47. በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ጩኸቱን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን እየተጣራ ነው!” አሉ።

48. ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጦ ሰፍነግ በመውሰድ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ነከረው፤ ሰፍነጉንም በሸምበቆ ዘንግ ጫፍ ላይ በማድረግ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት።

49. የቀሩት ግን፣ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያድነው እናያለን!” አሉ።

50. ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ።

51. በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድር ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጣጠቁ፤

52. መቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩትም ብዙዎች ቅዱሳን ተነሡ፤

53. ከመቃብርም በመውጣት ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩ።

54. የመቶ አለቃውና አብረውት ኢየሱስን ይጠብቁት የነበሩት የመሬት መናወጡንና የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው፤ ይህስ፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አሉ።

55. ከገሊላ የመጡና ኢየሱስን በሚያስፈልገው ነገር ለማገልገል የተከተሉት ብዙ ሴቶች ሁኔታውን ከርቀት እየተመለከቱ በአካባቢው ነበሩ።

ማቴዎስ 27