ማቴዎስ 27:23-40 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን ክፉ ነገር አድርጎአል?” በማለት ጠየቃቸው።እነርሱ ግን አብዝተው እየጮኹ፣ “ይሰቀል!” አሉ።

24. ጲላጦስ ሁኔታው ሽብር ከማስነሣት በስተቀር ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን ተመልክቶ፣ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የራሳችሁ ነው” በማለት ውሃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጆቹን ታጠበ።

25. ሕዝቡም በሙሉ፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን!” ብለው መለሱ።

26. በዚህ ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።

27. ከዚያም የአገረ ገዥው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በዙሪያው አሰባሰቡ።

28. ልብሱን ገፈው ቀይ ልብስ አጠለቁለት፤

29. እሾኽ ጐንጕነው አክሊል በመሥራት ራሱ ላይ ደፉበት፤ የሸምበቆ በትር በቀኝ እጁ በማስያዝ በፊቱ ተንበርክከው፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት አሾፉበት፤

30. ተፉበትም፤ የሸምበቆ በትሩን ከእጁ ወስደው ራሱ ላይ በሸምበቆው ደግመው ደጋግመው መቱት፤

31. ካሾፉበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈው የራሱን መጐናጸፊያ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ።

32. ይዘውትም ሲሄዱ ስምዖን ተብሎ የሚጠራ የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት።

33. ትርጕሙ፣ “የራስ ቅል ስፍራ” ከሆነው ጎልጎታ ከተባለው ቦታ ሲደርሱ፣

34. ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን ቀምሶ ሊጠጣው አልፈቀደም።

35. ከሰቀሉትም በኋላ ዕጣ ጥለው ልብሱን ተካፈሉ፤

36. በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። ከራስጌውም፣

37. “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው” የሚል የክስ ጽሑፍ አኖሩ።

38. ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ፣ አንዱ በግራው አብረውት ተሰቅለው ነበር።

39. መንገድ ዐላፊዎችም በኀይል እየተሳደቡና ራሳቸውን እየነቀነቁ፣

40. “ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን ውስጥ የምትሠራው፤ እስቲ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ በል ከመስቀል ውረድ!” ይሉት ነበር።

ማቴዎስ 27