ማቴዎስ 27:13-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. በዚህ ጊዜ ጲላጦስ፣ “ስንት ነገር አቅርበው እንደሚከሱህ አትሰማምን?” አለው።

14. እርሱ ግን አገረ ገዥው እስኪገረም ድረስ ለቀረበበት ክስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰም።

15. አገረ ገዥው ሕዝቡ በበዓሉ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው።

16. በዚያን ጊዜ በዐመፅ የታወቀ በርባን የሚባል እስረኛ ነበር።

17. ሕዝቡ እንደተሰበሰቡ ጲላጦስ፣ “ከበርባንና ክርስቶስ ከሚባለው ከኢየሱስ፣ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤

18. ጲላጦስም በቅናት አሳልፈው እንደሰጡት ያውቅ ነበርና።

19. በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፣ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ስለተሠቃየሁ፣ በዚያ ንጹሕ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት።

20. ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በርባን እንዲፈታላቸው ኢየሱስ ግን እንዲገደል ይለምኑ ዘንድ ሕዝቡን ያግባቡ ነበር።

21. አገረ ገዥውም፣ “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቀ።እነርሱም፤ “በርባንን!” በማለት መለሱ።

22. ጲላጦስም፣ “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስንስ ምን ላድርገው?” አላቸው።ሁሉም፣ “ይሰቀል!” አሉ።

23. ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን ክፉ ነገር አድርጎአል?” በማለት ጠየቃቸው።እነርሱ ግን አብዝተው እየጮኹ፣ “ይሰቀል!” አሉ።

24. ጲላጦስ ሁኔታው ሽብር ከማስነሣት በስተቀር ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን ተመልክቶ፣ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የራሳችሁ ነው” በማለት ውሃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጆቹን ታጠበ።

25. ሕዝቡም በሙሉ፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን!” ብለው መለሱ።

26. በዚህ ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።

27. ከዚያም የአገረ ገዥው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በዙሪያው አሰባሰቡ።

28. ልብሱን ገፈው ቀይ ልብስ አጠለቁለት፤

29. እሾኽ ጐንጕነው አክሊል በመሥራት ራሱ ላይ ደፉበት፤ የሸምበቆ በትር በቀኝ እጁ በማስያዝ በፊቱ ተንበርክከው፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት አሾፉበት፤

30. ተፉበትም፤ የሸምበቆ በትሩን ከእጁ ወስደው ራሱ ላይ በሸምበቆው ደግመው ደጋግመው መቱት፤

31. ካሾፉበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈው የራሱን መጐናጸፊያ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ።

ማቴዎስ 27