7. “በዚህ ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ።
8. ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው።
9. “አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው።
10. “ዘይት ሊገዙ እንደሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ አብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።
11. “ዘግየት ብለው ሌሎቹ ልጃገረዶች መጥተው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ አሉ።
12. “እርሱ ግን መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።
13. “እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።
14. “የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤
15. ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጒዞውን ቀጠለ።
16. አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውዬ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤
17. እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤
18. አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።
19. “የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ።
20. አምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።
21. “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
22. “እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።