ማቴዎስ 21:13-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን፣ ‘የዘራፊዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው።

14. በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዐይነ ስውሮችና ሽባዎች ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈወሳቸው።

15. ነገር ግን የካህናት አለቆችና የኦሪት ሕግ መምህራን ያደረጋቸውን ታምራትና፣ “ሆሣዕና፤ ለዳዊት ልጅ” እያሉ የሚጮኹትን ሕፃናት ባዩ ጊዜ በቍጣ ተሞሉ።

16. እነርሱም፣ “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህ” አሉት።ኢየሱስም፣ “አዎን እሰማለሁ፤ እንዲህ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” “ ‘ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ፣ ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ።’ ”

17. ትቶአቸው ከከተማው ወጣ፤ ወደ ቢታንያም ሄዶ በዚያው አደረ።

18. ኢየሱስ በማግስቱ ማለዳ ወደ ከተማዪቱ በመመለስ ላይ ሳለ ተራበ፤

19. በመንገድ ዳርም አንድ የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ ሲሄድ ከቅጠል በስተቀር ምንም ስላላገኘባት፣ “ከእንግዲህ ፍሬ አይኑርብሽ!” አላት፤ የበለሷ ዛፍ ወዲያውኑ ደረቀች።

20. ደቀ መዛሙርቱም የሆነውን አይተው በመደነቅ፣ “የበለሷ ዛፍ እንዴት ባንዴ ልትደርቅ ቻለች?” አሉ።

21. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩ፣ በበለሷ ዛፍ ላይ የሆነውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነቅለህ ባሕር ውስጥ ግባ’ ብትሉት እንኳ ይሆናል፤

22. እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።”

23. ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በማስተማር ላይ ሳለ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀርበው፣ “ይህን ሁሉ ነገር የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ሥልጣንስ የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት።

ማቴዎስ 21