2. “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ የሚሽሩት ለምንድ ነው? ምግብ ሲበሉኮ እጃቸውን አይታጠቡም” አሉት።
3. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተስ ለወጋችሁ ስትሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትሽራላችሁ?
4. እግዚአብሔር፣ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ በአባቱ ወይም በእናቱ ላይ ክፉ ቃል የሚናገር ይገደል’ ብሎ ሲያዝ፣
5. እናንተ ግን፣ ማንም ሰው አባቱን ወይም እናቱን፣ ‘ላደርግላችሁ የሚገባውን ማንኛውንም ነገር ለእግዚአብሔር መባ አድርጌ አቅርቤአለሁ’ ቢላቸው፣
6. ‘አንድ ሰው ይህን ካደረገ ዘንድ አባቱን ወይም እናቱን አክብሮአል’ ትላላችሁ። ስለዚህ ለወጋችሁ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ።
7. እናንት ግብዞች፤ ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ብሎ በትንቢት የተናገረው ትክክል ነው፤
8. “ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤
9. በከንቱ ያመልኩኛል፣ ትምህርታቸውም የሰው ሥርዓት ነው።’ ”
10. ሕዝቡን ወደ እርሱ ቀረብ እንዲሉ አድርጎ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙ አስተውሉም፤
11. ሰውን የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው እንጂ ወደ አፉ የሚገባው አይደለም።”
12. ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፣ “ፈሪሳውያን ያልኸውን ሰምተው እንደተቈጡ አወቅህ?” አሉት።
13. እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል።
14. ተዉአቸው፣ እነርሱ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውር መሪዎች ናቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ተያይዘው ገደል ይገባሉ።”
15. ጴጥሮስም፣ “ምሳሌውን አስረዳን” አለው።