ማቴዎስ 12:18-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. “እነሆ የመረጥሁት፣የምወደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ፣መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል።

19. አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ድምፁም በአደባባይ አይሰማም።

20. ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም፤የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም።

21. አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”

22. ከዚህ በኋላ በጋኔን የተያዘ ዕውርና ድዳ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ ኢየሱስም ፈወሰው፤ ሰውየውም ማየትና መናገር ቻለ።

23. ሕዝቡም ሁሉ ተደንቀው፣ “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ።

24. ነገር ግን ፈሪሳውያን ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “ይህ ሰው አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ብቻ መሆን አለበት” አሉ።

25. ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በእርሱ የተከፋፈለ መንግሥት ሁሉ ይወድቃል፤ እርስ በእርሱም የተከፋፈለ ከተማ ወይም ቤት አይጸናም።

26. ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፣ እርስ በእርሱ ተለያይቷል ማለት ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል?

27. እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በምን ሊያስወጧቸው ነው? ስለዚህ ልጆቻችሁ ይፈርዱባችኋል።

28. እኔ ግን አጋንንትን የማስወጣው በእግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች።

29. “ወይስ አንድ ሰው ወደ ኀይለኛ ሰው ቤት ገብቶ ንብረቱን ለመዝረፍ ቢፈልግ፣ አስቀድሞ ያንን ኀይለኛ ሰው ሳያስር እንዴት አድርጎ ይሳካለታል? ኋላም ቤቱን መበዝበዝ ይችላል።

ማቴዎስ 12