12. ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥምን? ስለዚህ በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዶአል” አላቸው።
13. ከዚያም ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እንደ ሌላኛውም እጁ ደህና ሆነለት።
14. ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጣ ብለው ኢየሱስን እንዴት እንደሚገድሉት ተማከሩ።
15. ኢየሱስ ሐሳባቸውን አውቆ ከዚያ ዘወር አለ። ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ ሕመምተኞችን ሁሉ ፈወሰ፤
16. ማንነቱን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።
17. ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤
18. “እነሆ የመረጥሁት፣የምወደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ፣መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል።
19. አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ድምፁም በአደባባይ አይሰማም።
20. ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም፤የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም።
21. አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”
22. ከዚህ በኋላ በጋኔን የተያዘ ዕውርና ድዳ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ ኢየሱስም ፈወሰው፤ ሰውየውም ማየትና መናገር ቻለ።
23. ሕዝቡም ሁሉ ተደንቀው፣ “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ።
24. ነገር ግን ፈሪሳውያን ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “ይህ ሰው አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ብቻ መሆን አለበት” አሉ።
25. ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በእርሱ የተከፋፈለ መንግሥት ሁሉ ይወድቃል፤ እርስ በእርሱም የተከፋፈለ ከተማ ወይም ቤት አይጸናም።
26. ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፣ እርስ በእርሱ ተለያይቷል ማለት ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል?