15. እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን በዚያች ከተማ ከሚደርሰው ቅጣት ይልቅ በሰዶምና በገሞራ የሚደርሰው ይቀላል።
16. “እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ።
17. “ሰዎች ይዘው ለፍርድ ወደ ሸንጎ ያቀርቧችኋል፤ በምኵራ ቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ስለዚህ ከእነርሱ ተጠንቀቁ።
18. በእኔ ምክንያት ወደ ገዦችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፤ በእነርሱና በአሕዛብም ፊት ምስክር ትሆናላችሁ።
19. በምትያዙበትም ጊዜ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያን ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል፤
20. በእናንተ የሚናገረው የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።
21. “ወንድም ወንድሙን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ አባትም ልጁን፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ያስገድሏቸዋልም።
22. ስለ ስሜ ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ ነገር ግን እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል።
23. በአንድ ስፍራ ሲያሳድዷችሁ ወደ ሌላ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የእስራኤልን ከተሞች ሳታዳርሱ የሰው ልጅ ይመጣል።
24. “ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፣ ሎሌም ከጌታው አይበልጥም፤