38. ዮሐንስም፣ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየን፣ እኛን ስለ ማይከተልም ከለከልነው” አለው።
39. ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “አትከልክሉት፤ ማንም በስሜ ታምር ሠርቶ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ መናገር አይችልም፤
40. የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋር ነውና፤
41. እውነት እላችኋለሁ፣ የክርስቶስ በመሆናችሁ በስሜ አንድ ኩባያ ውሃ የሚሰጣችሁ ሁሉ ዋጋውን አያጣም።”
42. “በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል።
43. ስለዚህ እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመሄድ፣ ጒንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤
44. በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና።
45. እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤
46. በገሃነም ትሉ አይሞትም እሳቱ አይጠፋምና።
47. ዐይንህ ብታሰናክልህ ጐልጒለህ አውጣት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል፤