ማርቆስ 9:32-50 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

32. እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

33. ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ቤት ከገባ በኋላም፣ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው።

34. እነርሱ ግን በመንገድ ላይ የተከራከሩት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው በሚል ስለ ነበር ዝም አሉ።

35. ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ጠርቶ፣ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ፣ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው።

36. ትንሽ ልጅ አምጥቶም በመካከላቸው አቆመ፤ አቅፎትም፣

37. “ከእነዚህ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበለኝ ሁሉ የሚቀበለው እኔን ሳይሆን የላከኝን ነው” አላቸው።

38. ዮሐንስም፣ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየን፣ እኛን ስለ ማይከተልም ከለከልነው” አለው።

39. ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “አትከልክሉት፤ ማንም በስሜ ታምር ሠርቶ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ መናገር አይችልም፤

40. የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋር ነውና፤

41. እውነት እላችኋለሁ፣ የክርስቶስ በመሆናችሁ በስሜ አንድ ኩባያ ውሃ የሚሰጣችሁ ሁሉ ዋጋውን አያጣም።”

42. “በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል።

43. ስለዚህ እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመሄድ፣ ጒንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤

44. በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና።

45. እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤

46. በገሃነም ትሉ አይሞትም እሳቱ አይጠፋምና።

47. ዐይንህ ብታሰናክልህ ጐልጒለህ አውጣት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል፤

48. “በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና፤

49. ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና።

50. “ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው ጨውነቱን ቢያጣ እንዴት መልሳችሁ ጣዕም እንዲኖረው ታደርጉታላችሁ? ጨው በውስጣችሁ ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።”

ማርቆስ 9