1. በዚያን ጊዜ፣ እንደ ገና ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። የሚበሉት ምንም ምግብ ስላልነበራቸው ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤
2. “ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ስለቈዩና የሚበሉትም ስለሌላቸው እነዚህ ሰዎች ያሳዝኑኛል፤
3. እንዲህ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ብሰዳቸው አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ስለሆኑ በመንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ።”
4. ደቀ መዛሙርቱም መልሰው፣ “በዚህ ምድረ በዳ እነዚህን ለመመገብ የሚያስችል እንጀራ ከወዴት ይገኛል?” አሉት።
5. እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት።
6. እርሱም፣ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራ ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቈርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አደሉት።
7. እንዲሁም ትንንሽ ዓሣዎች ነበሯቸው፤ እርሱም ዓሣዎቹን ባርኮ እንዲያድሏቸው አዘዘ።
8. ሕዝቡም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ የተረፈውን ቍርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ።
9. በዚያም አራት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ፤ ካሰናበታቸውም በኋላ፣
10. ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ዳልማኑታ ወደተባለ ስፍራ ሄደ።