5. በልባቸው ደንዳናነት አዝኖ በዙሪያው የቆሙትን በቍጣ ተመለከታቸውና ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ!” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እጁም ፍጹም ደኅና ሆነችለት።
6. ፈሪሳውያንም እንዴት ሊያጠፉት እንደሚችሉ ከሄሮድስ ወገን ከሆኑት ጋር መመካከር ጀመሩ።
7. ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላ የመጣ እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤
8. የሚሠራውን ነገር የሰሙ ሰዎችም ከይሁዳ፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስ፣ በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አገር እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ ወደ እርሱ መጡ።
9. የተሰበሰበውም ሕዝብ እንዳያጨናንቀው አነስተኛ የሆነ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።
10. ብዙዎችን ፈውሶ ስለ ነበር፣ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ ሊዳስሱት ይሽቀዳደሙ ነበር።
11. ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ቍጥር ከፊቱ እየወደቁ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” በማለት ይጮኹ ነበር።
12. እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጹ አጥብቆ ይገሥጻቸው ነበር።
13. ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠራቸው፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ።
14. ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፣ ለስብከትም ይልካቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለቱን ሾማቸው፤ ሐዋርያትም ብሎ ጠራቸው፤
15. አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው።
16. የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖን፣