ማርቆስ 3:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ብዙዎችን ፈውሶ ስለ ነበር፣ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ ሊዳስሱት ይሽቀዳደሙ ነበር።

11. ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ቍጥር ከፊቱ እየወደቁ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” በማለት ይጮኹ ነበር።

12. እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጹ አጥብቆ ይገሥጻቸው ነበር።

13. ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠራቸው፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ።

14. ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፣ ለስብከትም ይልካቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለቱን ሾማቸው፤ ሐዋርያትም ብሎ ጠራቸው፤

15. አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው።

16. የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖን፣

17. ቦአኔርጌስ ይኸውም፣ “የነጐድጓድ ልጆች” ብሎ የጠራቸው የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፤

18. እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርቶሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ተቀናቃኙ ስምዖን፣

19. እንዲሁም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።

20. ከዚያም ኢየሱስ ወደ አንድ ቤት ገባ፤ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪሳናቸው ድረስ ሕዝቡ እንደ ገና በብዛት ተሰበሰበ።

21. ሁኔታውን የሰሙ ዘመዶቹም፣ “አእምሮውን ስቶአል” በማለት ይዘውት ለመሄድ ወዳለበት መጡ።

22. ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም፣ “ብዔልዜቡል አድሮበታል፤ አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ።

ማርቆስ 3