4. ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ኢየሱስ ወዳለበት መቅረብ ስላልቻሉ፣ የቤቱን ጣራ እርሱ ባለበት በኩል ነድለው ቀዳዳ በማበጀት ሽባው የተኛበትን ዐልጋ በዚያ አወረዱ።
5. ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አንተ ልጅ፣ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል!” አለው።
6. በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍት ስለዚህ ነገር በልባቸው እያሰላሰሉ፣
7. “ይህ ሰው እንዴት እንዲህ ይላል? በአምላክ ላይ የስድብ ቃል እየተናገረ እኮ ነው! ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማን ኀጢአትን ሊያሰተሰርይ ይችላል?” ብለው አሰቡ።
8. ኢየሱስም ወዲያው በልባቸው የሚያስቡትን በመንፈሱ ተረድቶ፣ “እንዴት እንዲህ ታስባላችሁ?
9. ሽባውን፣ ‘ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና፣ ‘ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?
10. ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ” በማለት ሽባውን፣
11. “ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።
12. እርሱም ተነሥቶ ሁሉም እያዩት ዐልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ በስፍራው የነበሩትም ሁሉ በሁኔታው በመደነቅ፣ “የዚህ ዐይነት ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም!” በማለት ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ።
13. ኢየሱስም ዳግም ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወጣ፤ ሕዝቡም በብዛት ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም አስተማራቸው።
14. በዚያም ሲያልፍ የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በቀረጥ መቀበያው ስፍራ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።