ማርቆስ 15:29-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አዬ! ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ አንተ ነህ፤

30. እስቲ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን።”

31. እንዲሁም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በማሾፍ እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም፤

32. አይተን እናምን ዘንድ ይህ ክርስቶስ፣ ይህ የእስራኤል ንጉሥ እስቲ ከመስቀል ይውረድ።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉትም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር።

33. ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።

34. በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፣ “ኤሎሄ፣ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው።

35. በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ።

36. ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የሆመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ ከዚያም፣ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ።

37. ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ።

38. የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ።

39. በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አለ።

ማርቆስ 15