17. ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊል ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበት።
18. ከዚያም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ እጅ ነሡት፤
19. ራሱንም በበትር መቱት፤ ተፉበትም፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት።
20. ካፌዙበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ የገዛ ልብሱን አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።
21. የአሌክሳንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት።
22. ከዚያም ኢየሱስን፣ ትርጒሙ “የራስ ቅል ስፍራ” ወደተባለ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት።
23. ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅም ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም።
24. ከዚያም ሰቀሉት፤ እያንዳንዱም ምን እንደሚደርሰው ለማወቅ ዕጣ ተጣጥለው ልብሱን ተከፋፈሉ።
25. ሲሰቅሉትም ጊዜው ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ነበረ።
26. የክሱ ጽሑፍም፣ “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ነበር።
27. ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ።
28. መጽሐፍ፣ “ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ” ያለውም በዚሁ ተፈጸመ።
29. በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አዬ! ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ አንተ ነህ፤