ማርቆስ 14:55-67 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

55. የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም።

56. ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፣ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም።

57. አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤

58. “ይህ፣ ‘የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።”

59. ይህም ሆኖ፣ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም።

60. ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፣ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድን ነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው።

61. ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም።ሊቀ ካህናቱም እንደ ገና፣ የቡሩኩ ልጅ፣ ክርስቶስ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው።

62. ኢየሱስም፣ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፣ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ።

63. ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፣ እንዲህ አለ፤ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል?

64. ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ፣ ምን ይመስላችኋል?”፤እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት።

65. በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፣ “እስቲ ትንቢት ተናገር!” ይሉት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።

66. ጴጥሮስ በግቢው ውስጥ በታችኛው በኩል ሳለ፣ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤

67. ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኵር ብላ ተመለከተችውና፣“አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው።

ማርቆስ 14