13. በእኔ ምክንያት በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል።
14. “ ‘የጥፋት ርኵሰት’ ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤
15. በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤
16. በእርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ።
17. በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!
18. ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤
19. በመጀመሪያ እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ፣ እንዲሁ ደግሞም ወደ ፊት አቻ የሌለው ታላቅ መከራ ይሆናልና።
20. ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሮአል።
21. በዚያን ጊዜ ማንም፣ ‘እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው?’ ቢላችሁ ወይም፣ ‘እነሆ፤ እዚያ ነው’ ቢላችሁ አትመኑ።
22. ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፣ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፣ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ።
23. ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ።
24. “በዚያን ጊዜ፣ ከመከራው በኋላ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፣ “ ‘ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤
25. ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ።’
26. “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል።