ማርቆስ 11:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ።

17. ሲያስተምራቸውም፣ “ ‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው።

18. የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና።

19. በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ።

20. በማግስቱ ጠዋት በመንገድ ሲያልፉ፣ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ።

21. ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምሃት በለስ ደርቃለች” አለው።

22. ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “በእግዚአብሔር እመኑ፤

23. እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና ይህንንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል።

24. ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደ ተቀበላችሁት አድርጋችሁ ብታምኑ ይሆንላችኋል።

25. እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ፣ የሰማዩ አባታችሁ ኀጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ፣ እናንተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ።

ማርቆስ 11