14. ከዚያም ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ።
15. ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤
16. ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ።
17. ሲያስተምራቸውም፣ “ ‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው።
18. የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና።
19. በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ።
20. በማግስቱ ጠዋት በመንገድ ሲያልፉ፣ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ።
21. ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምሃት በለስ ደርቃለች” አለው።
22. ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “በእግዚአብሔር እመኑ፤
23. እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና ይህንንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል።
24. ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደ ተቀበላችሁት አድርጋችሁ ብታምኑ ይሆንላችኋል።