32. ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ተገረሙ፣ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤
33. እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤
34. ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፣ ይገርፉታል፣ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”
35. ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት።
36. እርሱም፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
37. እነርሱም፣ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት።
38. ኢየሱስም፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፣ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አላቸው።
39. እነርሱም፣ “አዎን እንችላለን” አሉት።ኢየሱስም፣ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤
40. ነገር ግን በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ለተዘጋጀላቸው የሚሆን እንጂ እኔ የምሰጠው ነገር አይደለም” አላቸው።
41. ዐሥሩ ይህን ሲሰሙ፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መቈጣት ጀመሩ።
42. ኢየሱስም በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ አለቆች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፤ ሹሞቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ ታውቃላችሁ፤
43. በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤
44. ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤
45. የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና።”
46. ከዚህ በኋላ ወደ ኢያሪኮ መጡ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጡ ዐይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።
47. እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር።