ሚልክያስ 2:8-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እናንተ ግን ከመንገዱ ወጥታችኋል፤ በትምህርታችሁም ብዙዎች እንዲሰናከሉ አድርጋችኋል፤ የሌዊንም ኪዳን አፍርሳችኋል” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

9. “ስለዚህ በመንገዴ ስላልሄዳችሁና በትምህርታችሁም አድልዎ ስላደረጋችሁ፣ በሰዎች ሁሉ ፊት እንድትናቁና እንድትዋረዱ አድርጌአችኋለሁ።”

10. ሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለንምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? ታዲያ እርስ በርሳችን ታማኝነት በማጒደል የአባቶቻችንን ኪዳን ለምን እናረክሳለን?

11. ይሁዳ አልታመነም፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌምም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሞአል፤ ይሁዳ የባዕድ አምላክ ሴት ልጅ በማግባት እግዚአብሔር የሚወደውን መቅደስ አርክሶአል።

12. ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ቢሆን፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ቊርባን ቢያመጣም እንኳ፣ እግዚአብሔር ከያዕቆብ ድንኳን ያስወግደው።

ሚልክያስ 2