ሚልክያስ 2:10-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለንምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? ታዲያ እርስ በርሳችን ታማኝነት በማጒደል የአባቶቻችንን ኪዳን ለምን እናረክሳለን?

11. ይሁዳ አልታመነም፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌምም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሞአል፤ ይሁዳ የባዕድ አምላክ ሴት ልጅ በማግባት እግዚአብሔር የሚወደውን መቅደስ አርክሶአል።

12. ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ቢሆን፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ቊርባን ቢያመጣም እንኳ፣ እግዚአብሔር ከያዕቆብ ድንኳን ያስወግደው።

13. ሌላው የምታደርጉት ነገር ደግሞ፣ የእግዚአብሔርን መሠዊያ በእንባ ታጥለቀልቃላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቊርባናችሁን ስለ ማይመለከትና በደስታም ከእጃችሁ ስለማይቀበል ታለቅሳላችሁ፤ ትጮኻ ላችሁም።

14. እናንተም፣ “ለምን ይህ ሆነ?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ። ይህ የሆነው የትዳር ጓደኛህን፣ አጋርህንና የቃል ኪዳን ሚስትህን፣ አታለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በወጣትነት ሚስትህ መካከል ላለው ቃል ኪዳን ምስክር ስለ ሆነ ነው።

ሚልክያስ 2