መዝሙር 89:30-47 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. “ልጆቹ ሕጌን ቢተዉ፣ደንቤን ባይጠብቁ፣

31. ሥርዐቴን ቢጥሱ፣ትእዛዜንም ባያከብሩ፣

32. ኀጢአታቸውን በበትር፣በደላቸውን በጅራፍ እቀጣለሁ።

33. ምሕረቴን ግን ከእርሱ አላርቅም፤ታማኝነቴንም አላጓድልበትም።

34. ኪዳኔን አላፈርስም፤ከአፌ የወጣውንም አላጥፍም።

35. አንድ ጊዜ በቅድስናዬ ምያለሁና፣ዳዊትን አልዋሸውም።

36. የዘር ሐረጉ ለዘላለም፣ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሓይ ጸንቶ ይኖራል፤

37. በሰማይ ታማኝ ምስክር ሆና እንደምትኖረው፣እንደ ጨረቃ እርሱ ለዘላለም ይመሠረታል።” ሴላ

38. አሁን ግን ናቅኸው፤ ጣልኸውም፤የቀባኸውንም እጅግ ተቈጣኸው።

39. ከባሪያህ ጋር የገባኸውን ኪዳን አፈረስህ፤የክብር ዘውዱን ትቢያ ላይ ጥለህ አቃለልኸው።

40. ቅጥሩን ሁሉ አፈራረስህ፤ምሽጉንም ደመሰስህ።

41. ዐላፊ አግዳሚው ሁሉ ዘረፈው፤ለጎረቤቶቹ መዘባበቻ ሆነ።

42. የጠላቶቹን ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አደረግህ፤ባላንጣዎቹም ሁሉ ደስ አላቸው።

43. የሰይፉን ስለት አጠፍህ፤በጦርነትም ጊዜ አልረዳኸውም።

44. ግርማዊነቱን አጠፋህበት፤ዙፋኑንም ከዐፈር ደባለቅኸው።

45. የወጣትነት ዘመኑን አሳጠርኸው፤ዕፍረትንም አከናነብኸው። ሴላ

46. እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ እስከ መቼ ይሆናል? ራስህንስ ለዘላለም ትሰውራለህን?ቍጣህስ እንደ እሳት የሚነደው እስከ መቼ ነው?

47. ዘመኔ ምን ያህል አጭር እንደሆነች አስብ፤የሰውን ልጆች እንዲያው ለከንቱ ፈጠርሃቸው!

መዝሙር 89