መዝሙር 89:18-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ጋሻችን የእግዚአብሔር ነውና፤ንጉሣችንም የራሱ የእስራኤል ቅዱስ ነው።

19. በዚያን ጊዜ በራእይ ተናገርህ፤ታማኝ ሕዝብህንም እንዲህ አልህ፤“ኀያሉን ሰው ሥልጣን አጐናጸፍሁት፤ከሕዝብ መካከል የተመረጠውንም ከፍ ከፍ አደረግሁት።

20. ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፤በተቀደሰው ዘይቴም ቀባሁት።

21. እጄ ይደግፈዋል፤ክንዴም ያበረታዋል።

22. በጠላት አይበለጥም፤ክፉ ሰውም አይበግረውም።

23. ባላንጣዎቹን በፊቱ አደቅቃቸዋለሁ፤ጠላቶቹንም እቀጠቅጣለሁ።

24. ታማኝነቴና ምሕረቴ ከእርሱጋር ይሆናል፤በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል።

25. እጁን በባሕር ላይ፣ቀኝ እጁንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ።

26. እርሱም፣ ‘አንተ አባቴ ነህ፤አምላኬና መዳኛ ዐለቴም ነህ’ ብሎ ይጠራኛል።

27. እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፤ከምድር ነገሥታትም በላይ ከፍ ይላል።

28. ምሕረቴንም ለዘላለም ለእርሱ እጠብቃለሁ፤ከእርሱ ጋር የገባሁት ኪዳንም ጸንቶ ይኖራል።

መዝሙር 89