መዝሙር 69:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሞኝነቴን ታውቃለህ፤በደሌም ከአንተ የተሰወረ አይደለም።

6. ጌታ የሰራዊት አምላክ ሆይ፤አንተን ተስፋ የሚያደርጉ፣በእኔ ምክንያት አይፈሩ፤የእስራኤል አምላክ ሆይ፤አንተን አጥብቀው የሚሹ፣ከእኔ የተነሣ አይዋረዱ።

7. ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፤እፍረትም ፊቴን ሸፍኖአልና።

8. ለወንድሞቼ እንደ ባዕድ፣ለእናቴም ልጆች እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው።

9. የቤትህ ቅናት በላችኝ፤የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ዐርፎአል።

10. ነፍሴን በጾም ባስመረርሁ ጊዜ፣እነርሱ ሰደቡኝ።

11. ማቅ በለበስሁ ጊዜ፣መተረቻ አደረጉኝ።

12. በቅጥሩ ደጅ ለሚቀመጡት የመነጋገሪያ ርእስ፣ለሰካራሞችም መዝፈኛ ሆንሁ።

13. እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በወደድኸው ሰዓት፣ወደ አንተ እጸልያለሁ፤አምላክ ሆይ፤ በታላቅ ምሕረትህ፣በማዳንህም እርግጠኝነት መልስልኝ።

14. ከረግረግ አውጣኝ፤እሰጥም ዘንድ አትተወኝ፤ከጥልቅ ውሃ፣ከእነዚያ ከሚጠሉኝ ታደገኝ።

15. ጐርፍ አያጥለቅልቀኝ፤ጥልቅ ውሃም አይዋጠኝ፤ጒድጓዱም ተደርምሶ አይዘጋብኝ።

መዝሙር 69