መዝሙር 69:16-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ በጎ ናትና ስማኝ፤እንደ ርኅራኄም ብዛት መለስ በልልኝ።

17. ፊትህን ከባሪያህ አትሰውር፤ጭንቅ ውስጥ ነኝና ፈጥነህ መልስልኝ።

18. ወደ እኔ ቀርበህ ታደገኝ፤ስለ ጠላቶቼም ተቤዠኝ።

19. የደረሰብኝን ስድብ፣ ዕፍረትና ውርደት ታውቃለህ፤ጠላቶቼንም አንድ በአንድ ታውቃቸዋለህ።

20. ስድብ ልቤን ጐድቶታል፤ተስፋዬም ተሟጦአል፤አስተዛዛኝ ፈለግሁ፤ አላገኘሁምም፤አጽናኝም ፈለግሁ፤ አንድም አልነበረም።

21. ምግቤን ከሐሞት ቀላቀሉ፤ለጥማቴም ሆምጣጤ ሰጡኝ።

22. የቀረበላቸው ማእድ ወጥመድ ይሁንባቸው፤ለማኅበራቸውም አሽክላ ይሁን።

23. ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፤ጀርባቸውም ዘወትር ይጒበጥ።

24. መዓትህን በላያቸው አፍስስ፤የቍጣህም መቅሠፍት ድንገት ይድረስባቸው።

25. ሰፈራቸው ባድማ ይሁን፤በድንኳኖቻቸው የሚኖር አይገኝ፤

26. አንተ የመታኻቸውን አሳደዋልና፤ያቈሰልኻቸውንም ሥቃያቸውን አባብሰዋል።

27. በበደላቸው በደል ጨምርባቸው፤ወደ ጽድቅህም አይግቡ።

መዝሙር 69