7. የልጅነቴን ኀጢአት፣መተላለፌንም አታስብብኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ ብዛት፣እንደ ምሕረትህም መጠን ዐስበኝ።
8. እግዚአብሔር መልካምና ቅን ነው፤ስለዚህ ኀጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።
9. ዝቅ ያሉትን በፍትሕ ይመራቸዋል፤ለትሑታንም መንገዱን ያስተምራቸዋል።
10. ኪዳኑንና ሥርዐቱን ለሚጠብቁ፣ የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ናቸው።
11. እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአቴ ታላቅ ነውና፣ስለ ስምህ ይቅር በልልኝ።
12. እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው?በተመረጠለት መንገድ ያስተምረዋል።
13. ዘመኑን በተድላ ደስታ ያሳልፋል፤ዘሩም ምድርን ይወርሳል።
14. እግዚአብሔር ምስጢሩን ከሚፈሩት ወዳጆቹ አይሰውርም፤ኪዳኑንም ይገልጥላቸዋል።
15. ዐይኖቼ ሁል ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው፤እግሮቼን ከወጥመድ የሚያላቅቃቸው እርሱ ነውና።
16. እኔ ብቸኛና የተጨነቅሁ እንደ መሆኔ፣ወደ እኔ ተመለስ፤ ምሕረትም አድርግልኝ።
17. የልቤ መከራ በዝቶአል፤ከጭንቀቴ ገላግለኝ።
18. ጭንቀቴንና መከራዬን ተመልከት፤ኀጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።