መዝሙር 119:141-151 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

141. እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤ነገር ግን መመሪያህን አልዘነጋሁም።

142. ጽድቅህ ዘላለማዊ ጽድቅ ነው፤ሕግህም እውነት ነው።

143. መከራና ሥቃይ ደርሶብኛል፤ነገር ግን ትእዛዝህ ደስታዬ ነው።

144. ምስክርነትህ ለዘላለም የጽድቅ ምስክርነት ነው፤በሕይወት እኖር ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።

145. እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ እጮኻለሁና መልስልኝ፤ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ።

146. ወደ አንተ እጣራለሁና አድነኝ፤ምስክርነትህንም እጠብቃለሁ።

147. ትረዳኝ ዘንድ ጎሕ ሳይቀድ ተነሥቼ እጮኻለሁ፤ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።

148. ቃልህን አሰላስል ዘንድ፣ዐይኔ ሌሊቱን ሙሉ ሳይከደን ያድራል።

149. እንደ ቸርነትህ መጠን ድምፄን ስማ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ሕግህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።

150. ደባ የሚያውጠነጥኑ ወደ እኔ ቀርበዋል፤ከሕግህ ግን የራቁ ናቸው።

151. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ቅርብ ነህ፤ትእዛዛትህም ሁሉ እውነት ናቸው።

መዝሙር 119