መዝሙር 107:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።

14. ከጨለማና ከጥልማሞት አወጣቸው፤እስራታቸውንም በጠሰላቸው።

15. እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ፣ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤

16. እርሱ የናሱን በሮች ሰብሮአልና፤የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጦአል።

17. አንዳንዶቹ ከዐመፃቸው የተነሣ ቂሎች ሆኑ፤ከበደላቸው የተነሣ ችግር ውስጥ ገቡ።

18. ሰውነታቸው የምግብ ዐይነት ሁሉ ተጸየፈች፤ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ።

19. በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።

20. ቃሉን ልኮ ፈወሳቸው፤ከመቃብርም አፋፍ መለሳቸው።

21. እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ፣ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤

22. የምስጋናም መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ሥራውንም ደስ በሚል ዝማሬ ይግለጹ።

መዝሙር 107