መዝሙር 106:4-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እግዚአብሔር ሆይ፤ ለሕዝብህ ሞገስ ስታድል አስበኝ፤በምታድናቸውም ጊዜ ርዳኝ፤

5. ይኸውም የምርጦችህን ብልጽግና አይ ዘንድ፣በሕዝብህ ደስታ ደስ ይለኝ ዘንድ፣ከርስትህም ክብር የተነሣ እጓደድ ዘንድ ነው።

6. እኛም እንደ አባቶቻችን ኀጢአት ሠራን፤በደልን፤ ክፉም አደረግን።

7. አባቶቻችን በግብፅ ሳሉ፣ታምራትህን አላስተዋሉም፤የምሕረትህን ብዛት አላሰቡም፤በባሕሩ አጠገብ፣ ገና ቀይ ባሕር አጠገብ ዐመፁብህ።

8. እርሱ ግን የኀይሉን ታላቅነት ለማሳወቅ፣ስለ ስሙ አዳናቸው።

9. ቀይ ባሕርን ገሠጸ፤ እርሱም ደረቀ፤በምድረ በዳ እንደሚታለፍ በጥልቅ ውሃ መካከል መራቸው።

10. ከባለጋራቸው እጅ አዳናቸው፤ከጠላትም እጅ ታደጋቸው።

11. ባላንጦቻቸውን ውሃ ዋጣቸው፤ከእነርሱም አንድ አልተረፈም።

12. ከዚህ በኋላ የተስፋ ቃሉን አመኑ፤በዝማሬም አመሰገኑት።

13. ነገር ግን ያደረገውን ወዲያውኑ ረሱ፤በምክሩም ለመሄድ አልታገሡም።

14. በምድረ በዳ እጅግ መመኘት አበዙ፤በበረሓም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት።

15. እርሱም የለመኑትን ሰጣቸው፤ዳሩ ግን የሚያኰሰምን ሕመም ሰደደባቸው።

16. በሰፈር በሙሴ ላይ፣ ለእግዚአብሔር በተቀደሰውም በአሮን ላይ ቀኑ።

17. ምድር ተከፍታ ዳታንን ዋጠች፤የአቤሮንን ወገን ሰለቀጠች።

18. እሳት በጉባኤያቸው መካከል ነደደ፤ነበልባሉም ክፉዎችን ፈጅቶ አስወገደ።

19. በኮሬብ ጥጃ ሠሩ፤ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ።

20. ክብራቸው የሆነውንም ሣር በሚበላ፣በበሬ ምስል ለወጡ።

21. በግብፅ ታላቅ ነገር ያደረገውን፣ያዳናቸውን አምላክ ረሱ፤

22. እርሱ ግን በካም ምድር ድንቅ ሥራ፣በቀይ ባሕርም አስደናቂ ነገር አደረገ።

23. ስለዚህ በመቅሠፍቱ እንዳያጠፋቸው ይመለስ ዘንድ፣እርሱ የመረጠው ሙሴ በመካከል ገብቶ፣በፊቱ ባይቆም ኖሮ፣እንደሚያጠፋቸው ተናግሮ ነበር።

24. ከዚያም በኋላ መልካሚቱን ምድር ናቁ፤የተስፋ ቃሉንም አላመኑም።

መዝሙር 106