7. እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው።
8. ኪዳኑን ለዘላለም፣ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺህ ትውልድ ያስታውሳል።
9. ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ኪዳን፣ለይስሐቅም በመሐላ የተሰጠውን ተስፋ አይረሳም።
10. ይህንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ፣ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አድርጎ አጸናለት፤
11. እንዲህም አለ፤ “የርስትህ ድርሻ አድርጌ፣የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ።”
12. በቍጥር አነስተኞች ሆነው ሳሉ፣እጅግ ጥቂትና ባይተዋሮች ሳሉ፣
13. ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ሲንከራተቱ፣ከአንዱ መንግሥት ወደ ሌላው ሲቅበዘበዙ፣
14. ማንም ግፍ እንዲፈጽምባቸው አልፈቀደም፤ስለ እነርሱም ነገሥታትን እንዲህ ሲል ገሠጸ፤
15. “የቀባኋቸውን አትንኩ፤በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።”
16. በምድሪቱ ላይ ራብን ጠራ፤የምግብንም አቅርቦት ሁሉ አቋረጠ፤
17. በባርነት የተሸጠውን ሰው፣ዮሴፍን ከእነርሱ አስቀድሞ ላከ።
18. እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ።
19. የተናገረው ቃል እስኪፈጸምለት፣ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው።
20. ንጉሥ ልኮ አስፈታው፤የሕዝቦችም ገዥ ነጻ አወጣው።
21. የቤቱ ጌታ፣የንብረቱም ሁሉ አስተዳዳሪ አደረገው፤
22. ይኸውም ሹማምቱን በራሱ መንገድ ይመራ ዘንድ፣ታላላቆቹንም ጥበብ ያስተምር ዘንድ ነበር።
23. እስራኤል ወደ ግብፅ ገባ፤ያዕቆብ በካም ምድር መጻተኛ ሆነ።
24. እግዚአብሔር ሕዝቡን እጅግ አበዛ፤ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው፤
25. ሕዝቡን እንዲጠሉ፣በባሪያዎቹም ላይ እንዲያሤሩ ልባቸውን ለወጠ።