1. ናዖድ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት ከፉ ድርጊት ፈጸሙ።
2. ስለዚህም እግዚአብሔር በሐጾር ሆኖ ይገዛ ለነበረው ለከነዓን ንጉሥ ለኢያቢስ አሳልፎ ሸጣቸው። የኢያቢስ ሰራዊት አዛዥ፣ በሐሮሼትሐጎይም የሚኖረው ሲሣራ ነበረ፤
3. እርሱም ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎች ስለ ነበሩት እስራኤላውያንን ሃያ ዓመት እጅግ አስጨነቃቸው፤ እነርሱም ይረዳቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
4. በዚያን ጊዜ የለፊዶት ሚስት ነቢዪቱ ዲቦራ በእስራኤል ላይ ፈራጅ ነበረች።
5. እርሷም በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር፣ በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዘንባባ ዛፍ ሥር ተቀምጣ ትፈርድ ነበር፤ እስራኤላውያንም ለፍርድ ወደ እርሷ ይመጡ ነበር።
6. ዲቦራ፣ በንፍታሌም ውስጥ ቃዴስ በተባለች ከተማ ይኖር የነበረውን የአቢኒኤምን ልጅ ባራቅን አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ያዝሃል፤ “ተነሣ፤ ከንፍታሌምና ከዛብሎን ዐሥር ሺህ ሰዎች ይዘህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፤