መሳፍንት 10:8-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እነርሱም በዚያን ዓመት ሰበሯቸው፤ አደቀቋቸውም፤ እስራኤላውያንን ሁሉ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው በገለዓድ ምድር፣

9. በአሞራውያን አገር ዐሥራ ስምንት ዓመት እንዲሁም አሞናውያን ይሁዳን፣ ብንያምንና የኤፍሬምን ቤት ለመውጋት ዮርዳኖስን ስለ ተሻገሩ እስራኤላውያን እጅግ ተጨነቁ።

10. ከዚያም እስራኤላውያን አንተን አምላካችንን በመተው የበኣልን አማልክት በማምለካችን አንተን በድለናል” ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።

11. እግዚአብሔርም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ግብፃውያን፣ አሞራውያን፣ አሞናውያን፣ ፍልስጥኤማውያን፣

12. ሲዶናውያን፣ አማሌቃውያንና ማዖናውያን አሠቃዩአችሁ፤ እናንተም እንድረዳችሁ ወደ እኔ ጮኻችሁ፤ ታዲያ እኔ ከእጃቸው አላዳንኋችሁምን?

13. እናንተ ግን እኔን ትታችሁ ሌሎች አማልክትን አመለካችሁ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ አላድናችሁም፤

14. ሂዱና ወደ መረጣችኋቸው አማልክት ጩኹ፤ መከራ በሚያገኛችሁ ጊዜ እስቲ ያድኗችሁ።”

15. እስራኤላውያንም እግዚአብሔርን፣ “ኀጢአት ሠርተናል፤ መልካም መስሎ የታየህን አድርግብን፤ እባክህን የዛሬን ብቻ አድነን” አሉት።

16. ከዚያም በመካከላቸው ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወገዱ፤ እግዚአብሔርንም አመለኩ፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ስትጐሳቈል ዝም ብሎ ማየት አልቻለም።

17. አሞናውያን ለጦርነት ዝግጁ ሆነው በገለዓድ በሰፈሩ ጊዜ፣ እስራኤላውያንም እንደዚሁ ተሰብስበው በምጽጳ ሰፈሩ።

18. የገለዓድ ሕዝብ አለቆችም እርስ በእርሳቸው፣ “በአሞናውያን ላይ ጦርነቱን የሚጀምር ሰው በገለዓድ ነዋሪዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሆናል” ተባባሉ።

መሳፍንት 10