1. በስድስተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ በአምስተኛው ቀን በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ፣ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ፣ በዚያ የጌታ እግዚአብሔር እጅ በላዬ መጣች።
2. እኔም አየሁ፤ እነሆ፤ የሰውን ልጅ የሚመስል ነበረ፤ ወገቡ ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ታች እንደ እሳት ያለ ነበር፤ ወገቡንም ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ላይ እንደ ጋለ ብረት ያበራ ነበር።
3. እርሱም እጅ መሳይ ዘርግቶ የራስ ጠጒሬን ያዘ፤ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል አነሣኝ፤ እርሱም ቅናት የሚያነሣው ጣዖት ወደ ቆመበት፣ ወደ ውስጠኛው አደባባይ መግቢያ ወደ ሰሜን በር ወደ ኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ራእይ ወሰደኝ።
4. እነሆ፤ በረባዳው ስፍራ በራእይ ያየሁት የእስራኤል አምላክ ክብር በዚያ ነበረ።
5. እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ወደ ሰሜን ተመልከት” አለኝ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ ከመሠዊያው በር በሰሜን በኩል መግቢያው ላይ ይህ የቅናት ጣዖት ነበረ።
6. ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ከመቅደሴ ያርቀኝ ዘንድ በዚህ የሚያደርገውን እጅግ አስጸያፊ ነገር ታያለህን? ከዚህም የባሰ አስጸያፊ ነገር ታያለህ” አለኝ።
7. ከዚያም በኋላ ወደ አደባባዩ መግቢያ አመጣኝ፤ እኔም ግንቡን ተመለከትሁ፤ ቀዳዳም ነበረበት።
8. እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ግንቡን ንደለው” አለኝ፤ እኔም ግንቡን ነደልሁት፤ አንድ በርም አገኘሁ።
9. እርሱም፣ “ግባና በዚህ የሚፈጽሙትን እጅግ የከፋ ርኵሰት ተመልከት አለኝ።
10. እኔም ገብቼ አየሁ፤ እነሆ በደረታቸው የሚሳቡ ፍጡራንና የርኵሳን አራዊት ዐይነት ሁሉ፣ የእስራኤልም ቤት ጣዖታት ሁሉ ዙሪያውን በግንቡ ላይ ተቀርጸው ነበር።
11. በእነዚህም ፊት ከእስራኤል ቤት ሰባ ሽማግሌዎች ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም የሳፋን ልጅ ያእዛንያ ቆሞ ነበር፤ እያንዳንዳቸውም በእጃቸው ጥና ይዘዋል፤ መልካም መዐዛ ያለው የዕጣን ጢስም እየተትጐለጐለ ይወጣ ነበር።
12. እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች እያንዳንዳቸው በጣዖታቸው ምስል ጓዳ ውስጥ በጨለማ የሚያደርጉትን አይተሃልን? እነርሱ፣ ‘እግዚአብሔር አያየንም፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአል” ይላሉ” አለኝ።