ሕዝቅኤል 48:20-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. አጠቃላይ ይዞታው በአራቱም ማእዘን እኩል ሲሆን፣ እያንዳንዱ ማእዘን ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ነው፤ ከከተማዪቱ ድርሻ ጋር የተቀደሰውን ክፍል ልዩ መባ በማድረግ ታስቀምጣላችሁ።

21. “በተቀደሰው ድርሻና በከተማዪቱ ቦታ ግራና ቀኝ ያለው ቀሪ ቦታ፣ ለገዡ ይሆናል፤ ይህም ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ከሆነው ከተቀደሰው ቦታ አንሥቶ በምሥራቅ በኩል እስከ ምሥራቁ ወሰን ይዘልቃል፤ በምዕራቡም በኩል እንዲሁ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ከሆነው ይዞታ አንሥቶ እስከ ምዕራቡ ወሰን ይዘልቃል። የየነገዱ ድርሻ ከሆነውም መሬት ጐን ለጐን የሚሄዱት ቦታዎች የገዡ ይሆናሉ። የተቀደሰው ቦታና መቅደሱ በመካከላቸው ይሆናሉ።

22. ስለዚህ የሌዋውያኑ ይዞታና የከተማዪቱ ይዞታ ለገዡ በተሰጠው ቦታ መካከል ይሆናል፤ የገዡ ቦታም በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል ይሆናል።

23. “የቀሩት ነገዶች ድርሻ እንደሚከተለው ይሆናል፤ ‘የብንያም ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ይዘልቃል።

24. “ ‘የስምዖን ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የስምዖንን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

25. “ ‘የይሳኮር ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የስምዖንን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

26. “ ‘የዛብሎን ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የይሳኮርን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

27. “ ‘የጋድ ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የዛብሎንን ግዛት ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

28. “ ‘የጋድ ደቡባዊ ወሰን ከታማር ደቡብ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውሆች ይደርሳል፤ የግብፅን ደረቅ ወንዝ ይዞ እስከ ታላቁ ባሕር ይዘልቃል።

29. “ ‘ለእስራኤል ነገዶች ርስት አድርጋችሁ የምታከፋፍሏት ምድር ይህች ናት፤ ድርሻዎቻቸውም እነዚህ ናቸው” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

30. “ ‘የከተማዪቱ መውጫ በሮች እነዚህ ናቸው፤ ከሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት ካለው በር አንሥቶ፣

31. የከተማዪቱ በሮች በእስራኤል ነገዶች ስም ይጠራሉ፤ በሰሜን በኩል ያሉት ሦስቱ በሮች የሮቤል ነገድ በር፣ የይሁዳ ነገድ በርና የሌዊ ነገድ በር ይሆናሉ።

32. “ ‘በምሥራቅ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት ባለው በር ሦስት በሮች ይኖራሉ፤ እነዚህም የዮሴፍ በር፣ የብንያም በርና የዳን በር ናቸው።

ሕዝቅኤል 48