10. ዓሣ አጥማጆች በወንዙ ዳር ይቆማሉ፤ ከዓይንጋዲ እስከ ዓይንኤግላይም ድረስ ያለው ቦታ መረብ መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣውም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣ፣ የተለያየ ዐይነት ይሆናል።
11. ነገር ግን ረግረጉና ዕቋሪው ውሃ ንጹሕ አይሆንም፤ ጨው እንደሆነ ይቀራል።
12. በወንዙም ዳርና ዳር፣ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶች ሁሉ ይበቅላሉ፤ ቅጠላቸው አይደርቅም፤ ፍሬ አልባም አይሆኑም። ከመቅደሱ የሚወጣው ውሃ ስለሚፈስላቸው በየወሩ ያፈራሉ፤ ፍሬያቸው ለምግብ፣ ቅጠላቸውም ለፈውስ ይሆናል።
13. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምድሪቱን ርስት አድርገህ ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ የምታከፋፍሉባቸው፣ ወሰኖች እነዚህ ናቸው፤ ዮሴፍ ሁለት ዕጣ ይኑረው።