9. “ ‘በተወሰኑት በዓላት የምድሪቱ ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት በሚቀርብበት ጊዜ፣ ይሰግድ ዘንድ በሰሜን በር የገባ ሁሉ በደቡብ በር ይውጣ፤ በደቡብ በር የገባም በሰሜኑ በር ይውጣ፤ በፊት ለፊቱ ባለው በር ይመለስ እንጂ ማንም በገባበት በር አይውጣ።
10. ገዡ በመካከላቸው በመሆን፣ ሲገቡ ይገባል፤ ሲወጡም ይወጣል።
11. “ ‘በበዓላትና በተወሰኑት በዓላት፣ ከወይፈኑ ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ፣ ከአውራ በጉም ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቍርባን ያቅርብ፤ ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ግን ሰውየው የወደደውን ያህል ይሁን፤ እያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይኑረው።
12. ገዡ በፈቃዱ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕትም ሆነ የኅብረት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ በምሥራቅ ትይዩ የሆነው በር ይከፈትለት፤ በሰንበት ቀን እንደሚያደርገው ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕቱንም ሆነ የኅብረት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ከዚያ በኋላ ይወጣል፤ በሩም ይዘጋል።
13. “ ‘በየቀኑ እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር አቅርብ፤ ይህንንም በየማለዳው ታቀርበዋለህ።
14. ከዚህም ጋር አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት መለወሻም የሚሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ ዘይት አድርገህ በየማለዳው የእህል ቍርባን አቅርብ፤ ይህን የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ማቅረብም የዘላለም ሥርዐት ነው።
15. ስለዚህ ዘወትር ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በየማለዳው የበግ ጠቦት፣ የእህል ቍርባንና ዘይት ይቅረብ።
16. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ገዡ ከርስቱ ላይ ከወንድ ልጆቹ ለአንዱ ስጦታ ቢያደርግ፣ ያ ስጦታ ለዘሩ የሚተላለፍ ነው፤ በውርስም ንብረታቸው ይሆናል።
17. ይሁን እንጂ ገዡ ከርስቱ ላይ ከባሪያዎቹ ለአንዱ ቢሰጥ፣ ባሪያው ነጻ እስከሚወጣበት ዓመት ድረስ የራሱ ሊያደርገው ይችላል፤ ከዚያም ርስቱ ለገዡ ይመለስለታል፤ ርስቱም ለወንድ ልጆቹ ብቻ የሚተላለፍ ይሆናል፤ የእነርሱም ነው።
18. ገዡ ከንብረታቸው በማፈናቀል፤ የትኛውንም የሕዝቡን ርስት መውሰድ አይገባውም፤ ለወንድ ልጆቹ ርስት መስጠት ያለበት ከራሱ ንብረት ነው፤ ይኸውም ከሕዝቤ ማንም ከርስቱ እንዳይነቀል ነው።’ ”
19. ከዚያም ያ ሰው በበሩ አጠገብ ባለው መግቢያ አድርጎ፣ ለሰሜን ትይዩ ወደሆኑት ወደ ካህናቱ የተቀደሱ ክፍሎች አመጣኝ፤ በምዕራቡም መዳረሻ ያለውን ቦታ አሳየኝ።