12. ገዡ በፈቃዱ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕትም ሆነ የኅብረት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ በምሥራቅ ትይዩ የሆነው በር ይከፈትለት፤ በሰንበት ቀን እንደሚያደርገው ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕቱንም ሆነ የኅብረት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ከዚያ በኋላ ይወጣል፤ በሩም ይዘጋል።
13. “ ‘በየቀኑ እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር አቅርብ፤ ይህንንም በየማለዳው ታቀርበዋለህ።
14. ከዚህም ጋር አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት መለወሻም የሚሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ ዘይት አድርገህ በየማለዳው የእህል ቍርባን አቅርብ፤ ይህን የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ማቅረብም የዘላለም ሥርዐት ነው።
15. ስለዚህ ዘወትር ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በየማለዳው የበግ ጠቦት፣ የእህል ቍርባንና ዘይት ይቅረብ።
16. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ገዡ ከርስቱ ላይ ከወንድ ልጆቹ ለአንዱ ስጦታ ቢያደርግ፣ ያ ስጦታ ለዘሩ የሚተላለፍ ነው፤ በውርስም ንብረታቸው ይሆናል።
17. ይሁን እንጂ ገዡ ከርስቱ ላይ ከባሪያዎቹ ለአንዱ ቢሰጥ፣ ባሪያው ነጻ እስከሚወጣበት ዓመት ድረስ የራሱ ሊያደርገው ይችላል፤ ከዚያም ርስቱ ለገዡ ይመለስለታል፤ ርስቱም ለወንድ ልጆቹ ብቻ የሚተላለፍ ይሆናል፤ የእነርሱም ነው።
18. ገዡ ከንብረታቸው በማፈናቀል፤ የትኛውንም የሕዝቡን ርስት መውሰድ አይገባውም፤ ለወንድ ልጆቹ ርስት መስጠት ያለበት ከራሱ ንብረት ነው፤ ይኸውም ከሕዝቤ ማንም ከርስቱ እንዳይነቀል ነው።’ ”
19. ከዚያም ያ ሰው በበሩ አጠገብ ባለው መግቢያ አድርጎ፣ ለሰሜን ትይዩ ወደሆኑት ወደ ካህናቱ የተቀደሱ ክፍሎች አመጣኝ፤ በምዕራቡም መዳረሻ ያለውን ቦታ አሳየኝ።
20. እርሱም፣ “ይህ ስፍራ ሕዝቡን ለመቀደስ መሥዋዕቱን ወደ ውጩ አደባባይ እንዳያወጡ፣ ካህናቱ የበደሉን መሥዋዕትና የኀጢአቱን መሥዋዕት የሚቀቅሉበት፣ የእህሉንም ቍርባን የሚጋግሩበት ቦታ ነው” አለኝ።
21. ከዚያም ወደ ውጩ አደባባይ አመጣኝ፤ በአራቱም ማእዘን ዙሪያ መራኝ፤ በእያንዳንዱም ማእዘን ሌላ አደባባይ አየሁ።
22. በውጩ አደባባይ ባለው በአራቱ ማእዘን የታጠሩ አደባባዮች አሉ፤ ርዝመታቸው አርባ ክንድ፣ ወርዳቸውም ሠላሳ ክንድ ነበር፤ በአራቱም ማእዘን ያሉት አደባባዮች እኩል ናቸው።
23. ከሥሩ ዙሪያውን ምድጃ የነበረበት፣ በአራቱም አደባባዮች ውስጥ ዙሪያ የድንጋይ ዕርከን ነበር።