4. ከዚያም ያ ሰው በሰሜኑ በር በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አመጣኝ፤ እኔም ተመለከትሁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞልቶት አየሁ፤ በግንባሬም ተደፋሁ።
5. እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥርዐት የምነግርህን ሁሉ በጥንቃቄ አስተውል፤ በሚገባ አድምጥ፤ ልብም በለው። የቤተ መቅደሱን መግቢያና የመቅደሱን መውጫዎች ሁሉ አስተውል፤
6. ለዐመፀኛው የእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አስጸያፊ ሥራችሁ ከእንግዲህ ያብቃ!
7. ከአስጸያፊ ሥራችሁም ሌላ ምግብ፣ ስብና ደም ስታቀርቡ ልባቸውንና ሥጋቸውን ያልተገረዙትን እንግዶች ወደ መቅደሴ በማስገባት ቤተ መቅደሴን አረከሳችሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አፈረሳችሁ።
8. እናንተ ራሳችሁ ማድረግ የሚገባችሁን ቅዱሳት ሥርዐቶቼን በመፈጸም ፈንታ ባዕዳንን በኀላፊነት በመቅደሴ አስቀመጣችሁ።
9. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ ባዕድ በእስራኤላውያን መካከል የሚኖር ቢሆንም እንኳ ወደ መቅደሴ አይግባ።
10. ‘ “እስራኤል እኔን ከመከተል በራቁ ጊዜ፣ ከእኔ የራቁትና ጣዖቶቻቸውን በመከተል የተቅበዘበዙት ሌዋውያን የኀጢአታቸውን ዕዳ ይሸከማሉ።
11. የቤተ መቅደሱ በር ኀላፊ በመሆንና በእርሱም ውስጥ በማገልገል፣ መቅደሴን ሊያገለግሉ ይችላሉ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ዐርደው ስለ ሕዝቡ ሊሠዉ፣ በፊታቸው ሊቆሙና ሊያገለግሏቸው ይችላሉ።