14. ያም ሆኖ የቤተ መቅደሱን ሥራ በኀላፊነት እንዲሠሩ፣ በውስጡ የሚከናወኑትንም ሥራዎች ሁሉ እንዲቈጣጠሩ አደርጋቸዋለሁ።
15. ‘ “ነገር ግን እስራኤላውያን ከመንገዴ ስተው በወጡ ጊዜ፣ የመቅደሴን ሥራ በታማኝነት ያከናወኑት የሳዶቅ ዘርና ሌዋውያን የሆኑት፣ በፊቴ ቀርበው ያገለግሉኛል፤ በፊቴ ቆመው የስብና የደም መሥዋዕት ያቀርቡልኛል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16. እነርሱ ብቻ ወደ መቅደሴ ይገባሉ፤ እነርሱ ብቻ በፊቴ ሊያገለግሉ፣ ሥርዐቴንም ሊፈጽሙና ወደ ገበታዬ ሊቀርቡ ይችላሉ።
17. ‘ “ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሮች ሲገቡ፣ የበፍታ ፈትል ይልበሱ፤ በውስጠኛው አደባባይ በሮችም ሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያገለግሉ፣ ከበግ ጠጒር የተሠራ ልብስ አይልበሱ።
18. በራሳቸው ላይ ከበፍታ ፈትል የተሠራ ጥምጥም ያድርጉ፤ እንዲሁም ከበፍታ ፈትል የተሠራ ሱሪ በወገባቸው ላይ ይታጠቁ፤ እንዲያልባቸው የሚያደርግ ማንኛውንም ልብስ አይልበሱ።
19. ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ውጩ አደባባይ ሲወጡ፣ ሲያገለግሉበት የነበረውን ልብስ አውልቀው በተቀደሱት ክፍሎች በመተው ሌሎች ልብሶችን ይልበሱ፤ ይኸውም ሕዝቡን በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ነው።
20. ‘ “የራሳቸውን ጠጒር አይላጩት፤ ወይም አያርዝሙት፤ ነገር ግን ይከርክሙት።
21. ማንኛውም ካህን ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚገባበት ጊዜ የወይን ጠጅ አይጠጣ።
22. መበለቶችን ወይም ፈት ሴቶችን አያግቡ፤ ነገር ግን ከእስራኤል ዘር የሆኑ ድንግሎችን ወይም የካህናት ሚስቶች የነበሩትን መበለቶች ማግባት ይችላሉ።
23. በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ያለውን ልዩነት ለሕዝቤ ያስተምሩ፤ የረከሰውንና ያልረከሰውን እንዴት እንደሚለዩም ያሳዩአቸው።
24. ‘ “በማንኛውም ክርክር ካህናት ዳኞች ሆነው ያገልግሉ፤ በሥርዐቴም መሠረት ይወስኑ። የተለዩ በዓላቴን የሚመለከቱ ሕጎቼንና ሥርዐቶቼን ሁሉ ይጠብቁ፤ ሰንበታቴንም ቅዱስ አድርገው ይጠብቁ።
25. ‘ “ካህን ወደ ሞተ ሰው ሬሳ በመጠጋት ራሱን አያርክስ፤ ይሁን እንጂ ሟች አባቱ ወይም እናቱ፣ ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ፣ ወንድሙ ወይም ያላገባች እኅቱ ብትሆን፣ ራሱን ማርከስ ይችላል።
26. ከነጻም በኋላ፣ ሰባት ቀን መቈየት አለበት።